የቃል ኪዳኑ ታቦት በሰማይ

“በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ የኪዳኑም ታቦት ታየ” ራእ. 11፥19።

ቅዱስ ዮሐንስ በራእይ ስላየው ስለዚህ ቃል ልዩ ልዩ ትርጓሜዎችን የሰጡ ሊቃውንት አሉ።
ቤተ መቅደሱ ሰው የሆነው እግዚአብሔር ወልድ ነው ያሉ አሉ።
በወልድ ሰው መሆን የሰማያዊው አምላክ ለሰው ልጆች መገለጥን የሚያስረዳ መሆኑን በማብራራት ተተርጉሟል።

ተርጓሚው መነሻ ያደረገው ጌታ በቅዱስ ወንጌል “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛው ቀን መልሼ እሠራዋለሁ” ብሎ ቤተ መቅደስ ስለተባለ ሰውነቱ ያስተማረውን ትምህርት ነው ዮሐ. 2፥19።

ሌላ ተርጓሚ ደግሞ ለቆስጠንጢኖስ የታየውን መስቀል የኪዳን ታቦት ብሎ መጥራቱ ነው ብሎ ተርጉሟል።

ዛሬ በሰማይ ስለታየችው የኪዳን ታቦት ልነግራችሁ

ይህንን የወንጌላዊ ዮሐንስን ራእይ መነሻ አደረግሁት። ለሙሴ እንደተሰጡት ያለ የድንጋይ ጽላት ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ የከበረች አማናዊት ጽላት ዛሬ በሰማዩ ቤተ መቅደስ ታየች።

አባ ሕርያቆስ “ታቦት ዘዶር” የሚላት ነቢያት ሐዋርያት ከበዋት የሚቆሙ የአካላዊ ቃል መገኛ አማናዊት ታቦት ከእንግዲህ አይሁድ ሊያስወጧት ከማይቻላቸው የሰማይ ቤተ መቅደስ ገባች።

ነቢያት ዘመሩላት፥ የትንቢታቸው ፍጻሜ የተደረገው በእሷ ነውና።

ሐዋርያትም አመሰገኗት፥ በመላእክት እንኳን ሳይቀር እንዲፈርዱ የሚያስችለውን ስልጣን ሰጥቶ የሾማቸው ከእሷ የተወለደው ነውና 1ቆሮ. 6፥3።

መነኮሳትም አመሰገኗት፥ ገዳም ገብቶ ወደ ገዳም የመራቸውን የቆሮንቶሱን ባሕታዊ ያስገኘች እሷ ናትና።

ደናግልም አመሰገኗት፥ ከእመቤታችን በፊት ድንግልና ምን ዋጋ ነበረው? እመቤታችን ግን ድንግል ሆና በመገኘቷ ክርስቶስን በስጋ ወለደችልን፤ ደናግል በድንግልና ጸንተው በመገኘታቸው የድንግልናቸው ዋጋ አክሊል ሆኖ የተሰጣቸው ክርስቶስ ከእሷ የተገኘ ነውና።

ሰማዕታትም አመሰገኗት፥ ስለ ክርስቶስ መከራ መቀበልን የጀመረች እሷ ናትና።

እመቤታችን ወደ ሰማዩ ቤተ መቅደስ ገብታ በልጇ ቀኝ ስትቀመጥ “የወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝ ትቀመጣለች” መዝ. 45፥3 የሚለውን መዝሙር በሰማይ ያሉ ቅዱሳን ሁሉ ዘመሩት።

ገና በሦስት ዓመቷ ወደ አይሁድ ቤተ መቅደስ የገባችው በሊቀ ካህናቱ ፈቃድ ነበር፤ ዛሬ ደግሞ የማይሞተው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደሚያዝዝባት የሰማይ ቤተ መቅደስ ገባች።

ነቢያት ከትንቢታቸው ጋር በዚያ አሉ።
ኪሩቤል ከማይቋረጥ ምስጋናቸው ጋር በዚያ ይኖራሉ።
አብርሃም ይስሐቅ፣ ያዕቆብ ዳዊት ሰሎሞን ዕዝራ፣ ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ ሁሉም በዚያ አሉ።

የእመ አምላክ የቅድስት ድንግል ማርያም ልጆች በሙሉ እንኳን አደረሳችሁ!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

የነቢያት ትንቢት የተፈጸመው በዚህ ቦታ ነው፤ አንዱ ስለሁሉ የሞተው በዚህ ተራራ ላይ ነው።

ለዓለም ሁሉ ሕይወትን የሚሰጠውን ገደሉት።ታመው ሳሉ የፈወሳቸውን ሰቀሉት፤ “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” ብሎ ያዘዛቸውን መስቀል አሸከሙት። እንዴት ያለ ጭካኔ ነው?ለዐርባ ዓመታት በቃዴስ በረሀ ከዓለት የፈለቀ ውኃ

Read More »

ዓይነ ከርም(የጉዞ ማስታወሻ ክፍል አንድ)

በተራራማው የኤፍሬም ርስት የምትገኘው ዓይነ ከርም ከቦታው ስፋት የታሪኳ ብዛት ይገርመኛል የካህኑ ዘካርያስ ቤት በዚያ ይገኛል። “በ እግዚአብሔር ፊት ሁለቱም ጻድቃን ነበሩ” የተባለላቸው እነዚያ ቅዱሳን

Read More »